Thursday, June 9, 2016

ርዕስ አጣሁላት

‹‹ ርዕስ አጣሁላት ››
—————-አሃዱ ለህይወት!
አምላክ ፈጠረና አዳም ያሉት ፍጥረት፡፡
ብቸኛ መሆኑን ፈጣሪ አስተውሎ፤
ሔዋንን ሰራለት ግራ ጎንህ ብሎ፡፡
—————-ለኔም ለምስኪኑ!
ያለርሷ እንደማልችል አምላክም ተረድቶ፤
ሴትን ስለሰጠኝ ከአጥንቴ ሰርቶ፡፡
—————ይመስገን እላለሁ!
እርሷ ባትኖርልኝ ወዴት እሄዳለሁ፡፡
ለኔም እናት ሆናኝ ጡቷን ጠብቻለሁ፤
ሚስትም ሆናኝ ኖራ ዘሬን ተክቻለሁ፡፡
ሃገርም ስትሆነኝ በምድሯ ኖሬያለሁ፤
እትብቴን ሳላውቀው ከሴት ቀብሬያለሁ፡፡
———-ታድያ አንድ ቀን ጠዋት!
ግጥም ልጽፍላት ብእሬን አንስቼ፤
በሃሳብ እየዋተትኩ እጆቼን ቀስቼ፡፡
በሁለት ፊደላት ሴት ብለው ለጠሯት፤
ለሁሉ ነገሬ ርዕስ አጣሁላት፡፡
ከጠራው ሰማይ ወደ ላይ አናጋጠጥኩ፤
ግራ ገብቶኝ ሲቀር ወደ ምድር ቆፈርኩ፡፡
—————ለምን እንዳትሉኝ!
————–ርዕስ ፍለጋ፤
ህይወቴን በሙሉ ላጣሁላት ዋጋ፡፡
ልመና ገባሁኝ እርሷን ወደ ሰጠኝ፤
ለዚች ለሔዋኔ ተው ርዕስ ስጠኝ፡፡
ፈጣሪን ለምኜ እምቢ ከተባልኩኝ፤
ርዕስ የሌለው ግጥም መጻፍ ያዝኩኝ፡፡
ስንኜን ልቋጭ ስል በቃላት መረጣ፤
ቆይ ለሴት የሚሆን እንዴት ርዕስ ልጣ፡፡
ስብከነከን አይቶ ፈጣሪ እንዲህ አለኝ፤
“ሴት ላልካት አጥንትህ እኔም ርዕስ የለኝ፡፡
—————-ለምን እንዳትለኝ!
የጠፋው በጌን ፍለጋ እንደመጣሁ፤
በርሷ ማህጸን ነው መጀመርያ ያደርሁ፡፡
ከዛም ተወልጄ ከጡቷ ለጠባሁ፤
በእናትነት ፍቅሯ ከእቅፏ ለተኛሁ፤
እኔም ለፈጠርኳት ሴት ርዕስ አጣሁ፡፡”
ሲለኝ ተገርሜ ብእሬን እንደያዝኳት፤
ለዚች ሔዋኔ ግን ርዕስ አጣሁላት፡፡

ቢንያም ደምሴ

No comments:

Post a Comment