Friday, June 10, 2016

የመስቀል ለት ማታ

‹‹‹የመስቀል ለት ማታ ›››
ከደመራው ጀርባ ከችቦው ብልጭታ፤
ከመዘምራን ጋር ዝማሬ ተጫውታ፡፡
ከተካነችው ልጅ የሚያምር ፈገግታ፤
ካፈቀርኳት ቆንጆ የመስቀል ለት ማታ፡፡
ደመራው ሲለኮስ እሳት ተቀጣጥሎ፤
በሀሳብ ከወሰደኝ ፍቅሯ ልቤን ሰቅሎ፡፡
የመስቀል ወፍ ሆና ልቤን የሰጠኋት፤
በሐበሻ ቀሚስ ዘንጣ ያየኋት፤
የመውደዴ ረሀብ የፍቅሬ ጥማት ናት፡፡
………………………..
ወረብ ስትወርብ ከበሮ ስትመታ፤
ፍቅር ካስያዘችኝ የመስቀል ለት ማታ፤
አለብኝ ቀጠሮ ላግኛት ላንድ አፍታ፤
ታዳምጠው ስሜቴን የልቤን ትርታ፡፡
በእምነት ግንባሯ ላይ መስቀል አሰርታ፤
ከሄደችው ወጣት ትናንትና ማታ፤

አለብኝ ቀጠሮ የመስቀል ለት ማታ፡፡ 
         
ቢንያም ደምሴ

   

ላምባ

‹‹‹ላምባ ›››
ለራቀችው ቆንጆ ከደስታ መከዳ፤
ህመሟ ለሆነው የሀገር ሁሉ እዳ፡፡
ዛሬ ላይ ላጣናት በእምባ እየተራጨን፤
መፈክር የያዝነው በ'ርሷ ይብቃ ብለን፡፡
…………..አደባባይ መሀል ለተሰለፍንላት፤
………….ስሟን ከስም መርጠው በፀሎት ለሚሏት፤
…………..እስቲ እናልቅስላት፡፡
እንደሷ በሲቃ ወድቆ በየጓዳ፤
ስንቱ ወገኔ ሞተ ቆይ ስንቱስ ተጎዳ፡፡
የሳቅና ደስታው ቤት እንዳይሆን ባዶ፤
ኋላ እንዳይመጣብን ሀዘናችን ከብዶ፡፡
እኔ ለርሷ ላምባ ከመስመር ወጥቼ፤
ሞቷ እንዳይደገም በእህት ወንድሞቼ፡፡
ለነበረችው ልጅ ለወንድሟ ኩታ፤
ስትሞት ከጎናችን ኩላሊቷን አጥታ፡፡
በኛ የአንድነት ክንድ ሌሎቹ ይዳኑ፤
ሞት በበጺ ይብቃ ይለፍልን ቀኑ፡፡
ችግር አልፎ ደስታ ይምጣልን መረባ፤
ግን እስከዛው ድረስ ለዛች ቆንጆ ላምባ፡፡

        
ቢንያም ደምሴ


   

ዳግም ላልመለስ

‹‹‹ ዳግም ላልመለስ ›››
ፍቅር ማጣት ይዞኝ ስኖር ለብቻዬ፤
ቃልኪዳን ገባሁኝ በለጋው እድሜዬ፡፡
ልቤን ላጠነክር ዳግም ሰው እንዳይወድ፤
ተመልሶ እንዳይሄድ ወደ ፍቅር መንገድ፡፡
ፍቅር በሄደበት ላልሄድ ቃል ገብቼ፤
ባለፈበት መንገድ ላላልፍ ተገዝቼ፡፡
ብቸኝነት ጥሞኝ ስኖር ሁሉን ትቼ፤
በሰባራው ልቤ ስኖር ተደስቼ፡፡
………………………
አንቺ መጣሽና ቃሌን አሳጠፍሽኝ፤
ለቃሉ ያልቆመ ቃለ-ዓባይ አረግሽኝ፤
በሰባራው ልቤ በፍቅር ገዛሽኝ፡፡
…………..ግና ምን ያደርጋል!!!
ዳግም ላልመለስ ከሚል የልብ ወሬ፤
በፍቅርሽ ታከምኩኝ ቃሌን ሰባብሬ፡፡

                ቢንያም ደምሴ