Thursday, June 9, 2016

በሱስ ተነክሬ

በሱስ ተነክሬ
…………………………… ውዴ !
ካንቺ ከተለየሁ ያንጊዜ ጀምሬ፤
በፍቅርሽ እግረሙቅ ቃልኪዳን ታስሬ፤
ካስቀመጥሽኝ ቦታ ዛሬም ተገትሬ፤
አለሁኝ እላለሁ በሱስ ተነክሬ፡፡
የወሰደሽ መንገድ ያመጣሻል ብዬ፤
ትንባሆ እያቦለልኩ በአፍ ባፍንጫዬ፡፡
አንቺን ባቀፈ እጄ በርጫ ታቅፌበት፤
በሳመሽ ከንፈሬ መድዓ ስቤበት፤
……………………ሲጋራ ምጌበት፡፡
በጨዋታሽ ለዛ የሳቁት ጥርሶቼ፤
በፍቅራዊ ጉርሻሽ ተሞልተው ጉንጮቼ፤
…………………………….ነበር ያኔ እላለሁ፡፡
በያዝኩት መስተዋት ጥርሴ በልዞ እያየሁ፤
ጉንጬም በታርዚና ተወጥሮ እያየሁ፡፡
በስስት መልክሽን ያዩትም ዓይኖቼ፤
በጥቅሻሽ ብዛት አልቀው ቅንድቦቼ፡፡
መብራት ባነሰበት በቦግ እ…ል…ል…..ም ሀገር
…… … …… ………ለምንስ ይዋሻል፤
ግድባቸው እስኪያልቅ ፓውዛ ሊሆናቸው
…………………………አይኔ ፈጦልሻል፡፡
………………………ቀኑ እንደሁይመሻል፤
……………………..ትናንትም ይሸሻል፡፡
ከንፈሮቼ ጠቁረው ዛሬም ያጨሳሉ፤
በሲጋራው ጢስ ውስጥ አንቺን እየሳሉ፡፡
እጆቼም ሻከሩ ፊቴም ጠቋቆረ፤
በፍቅር ቃላትሽ ገጼ ውብ ነበረ፡፡
………….ሆኖም ግን የኔ ውድ!
ማንስ እንዳሰበው እንደ እቅዱ ኖረ፤
ከመጠበቅ በቀር ቀን እየቆጠረ፡፡
…………………….እኔም ህልሜ ነበር!
ካንቺ ጋር ተጋብቶ ባንድ ጎጆ ማደር፡፡
ውዴ እንዳሰብኩት ሁሉም መች ሆነና፤
ወጥተሸ ስትቀሪ በመራሽ ጎዳና፡፡
እኔም ራሴን ትቼ እቅዴን ቀይሬ፤
ዛሬ ድረስ አለሁ በሱስ ተነክሬ፡፡
          ✍✍✍ ✍✍✍

    ቢንያም ደምሴ

እናቴ ናት እሷ

‹‹ እናቴ ናት እሷ ››
እንዝርት አንጠልጥላ ባይንህ የምታያት፤
የእርሷን ፍቅር ከቶ ላልገልጸው በቃላት፡፡
ቀን ከሌት ስትሰሪ እኔንም ጸንሰሽ፤
ለኔ የኖርሽልኝ ያንቺን ኑሮ ትተሸ፡፡
ነፍሰ- ጡር እያለሽ ያየሽውን ስቃይ፤
እኔ ልጅሽ ዞሬ ወደ ኋላ እንዳላይ፡፡
ከራስሽ ተጣልተሸ ከሰው ያስታረቅሽኝ፤
ተራቁተሸ በመኖር ለኔ ያለበስሽኝ፤
ካፍሽ ላይ መልስሽ እንካ ጉረስ ያልሽኝ፡፡
እማይዬ ለኔ አንቺኮ ብዙ - ነሽ፤
በአንድ ማንነት ውስጥ ተስፋ ፍቅር ያለሽ፡፡
ክብርሽን ተገፈሽ የተዋረድሽውም፤
ለኔ እንደሁ አውቃለሁ ፍጹም አልረሳውም፡፡
አንገትሽን ደፍተሸ የሰው ፊት ያየሽው፤
በእሳት በነዲዱ የተንገረገብሽው፡፡
እንደ እናት እንደ አባት ሆነሽ ያሳደግሽኝ፤
እማዬ እዋዋዬ ውለታሽ አለብኝ፡፡
የእኔን ህመም ታመሽ ስቃዬን ተጋርተሸ፤
ትግስት ያስጨበጥሽኝ ተስፋን አስትመረሽ፡፡
ክብርሽን በጫጭቀው የሴት ልጅ ቢሉኝም፤
የጌታ እናት ሴት ነች ፍጹም አይከፋኝም፡፡
ይሰረዝ መኖሬ ይነጠቅ መክሊቴ፤
አንቺ ግን ኑሪልኝ እማይዬ እናቴ፡፡

          

ለምወድሽ እናቴ ብዙነሽ

ርዕስ አጣሁላት

‹‹ ርዕስ አጣሁላት ››
—————-አሃዱ ለህይወት!
አምላክ ፈጠረና አዳም ያሉት ፍጥረት፡፡
ብቸኛ መሆኑን ፈጣሪ አስተውሎ፤
ሔዋንን ሰራለት ግራ ጎንህ ብሎ፡፡
—————-ለኔም ለምስኪኑ!
ያለርሷ እንደማልችል አምላክም ተረድቶ፤
ሴትን ስለሰጠኝ ከአጥንቴ ሰርቶ፡፡
—————ይመስገን እላለሁ!
እርሷ ባትኖርልኝ ወዴት እሄዳለሁ፡፡
ለኔም እናት ሆናኝ ጡቷን ጠብቻለሁ፤
ሚስትም ሆናኝ ኖራ ዘሬን ተክቻለሁ፡፡
ሃገርም ስትሆነኝ በምድሯ ኖሬያለሁ፤
እትብቴን ሳላውቀው ከሴት ቀብሬያለሁ፡፡
———-ታድያ አንድ ቀን ጠዋት!
ግጥም ልጽፍላት ብእሬን አንስቼ፤
በሃሳብ እየዋተትኩ እጆቼን ቀስቼ፡፡
በሁለት ፊደላት ሴት ብለው ለጠሯት፤
ለሁሉ ነገሬ ርዕስ አጣሁላት፡፡
ከጠራው ሰማይ ወደ ላይ አናጋጠጥኩ፤
ግራ ገብቶኝ ሲቀር ወደ ምድር ቆፈርኩ፡፡
—————ለምን እንዳትሉኝ!
————–ርዕስ ፍለጋ፤
ህይወቴን በሙሉ ላጣሁላት ዋጋ፡፡
ልመና ገባሁኝ እርሷን ወደ ሰጠኝ፤
ለዚች ለሔዋኔ ተው ርዕስ ስጠኝ፡፡
ፈጣሪን ለምኜ እምቢ ከተባልኩኝ፤
ርዕስ የሌለው ግጥም መጻፍ ያዝኩኝ፡፡
ስንኜን ልቋጭ ስል በቃላት መረጣ፤
ቆይ ለሴት የሚሆን እንዴት ርዕስ ልጣ፡፡
ስብከነከን አይቶ ፈጣሪ እንዲህ አለኝ፤
“ሴት ላልካት አጥንትህ እኔም ርዕስ የለኝ፡፡
—————-ለምን እንዳትለኝ!
የጠፋው በጌን ፍለጋ እንደመጣሁ፤
በርሷ ማህጸን ነው መጀመርያ ያደርሁ፡፡
ከዛም ተወልጄ ከጡቷ ለጠባሁ፤
በእናትነት ፍቅሯ ከእቅፏ ለተኛሁ፤
እኔም ለፈጠርኳት ሴት ርዕስ አጣሁ፡፡”
ሲለኝ ተገርሜ ብእሬን እንደያዝኳት፤
ለዚች ሔዋኔ ግን ርዕስ አጣሁላት፡፡

ቢንያም ደምሴ